
ግንቦት 25/2017 ዓ.ም፤ ማይክሮሶፍት ኩባንያ ከጥቅምት 4/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለዊንዶዉስ 10 ተጠቃሚዎች የሚያቀርበዉን የደህንነት ማሻሻያ ድጋፎችን እንደሚያቋርጥ ገልጿል።
ከአራት / 4 /ወር በኋላ የቴክኒክ ድጋፍ እና የሶፍትዌር ዝመናዎችን ለዊንዶዉ-10 ምርቶች እንደማያቀርብ የገለጸዉ ኩባንያዉ የዊንዶውስ-10 ተጠቃሚዎች ቀኑ ከመድረሱ በፊት የዊንዶዉስ-10 ምርቶቻቸዉን ወደ ዊንዶዉስ-11 እንዲያሳድጉ መክሯል።
የዊንዶውስ-10 ምርትን እየተጠቀሙ መቆየት ለሚፈልጉ ደንበኞቹ የተራዘመ የደህንነት ማሻሻያ (ESU) ፕሮግራም እንደሚያቀርብ የጠቆመዉ ማይክሮሶፍት ይህ አገልግሎት ግን ክፍያ የሚጠየቅበት ነው ብሏል ።
የተራዘመ የደህንነት ማሻሻያ ፕሮግራም ማድረግ የሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት የዊንዶውስ-10 ምርቶቻቸዉ የደህንነት ማሻሻያ ለማይክሮሶፍት ክፍያ በመፈጸም ብቻ ድጋፉ ሳይቋረጥ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ መጠቀም እንደሚችሉ ገልጿል።
ኩባንያው እንዳለው መክፈል የማይችሉ ተጠቃሚዎች ግን ከዊንዶዉ-10 ወደ 11 በነጻ ለመሸጋገር የዊንዶዉስ-ቨርዥን 22H2 ተጠቃሚ መሆንና ዝቅተኛዉን የሃርድዌር ስፔስፊኬሽን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።
ይህንንም ለማረጋገጥ የሚከተሉትን አማራጮች በመጠቀም ማወቅ እንደሚችሉ አብራርቷል።
በቅድሚያ Start >Settings > Update & Security > Windows Update በመጨረሻም Check for updates የሚለዉን በመጫን ማረጋገጥ ይችላሉ።
በመሆኑም እርስዎ የዊንዶዉስ-10 እና ከዚያ በታች ያሉ ምርቶች ተጠቃሚ ከሆኑና ከፍለዉ የደህንነት ማሻሻያ ካላደረጉ / ካላራዘሙ / በስተቀር የሚጠቀሙበትን የዊንዶዉስ ምርት በማዘመን ከሶፍትዌር ዝመና ጋር በተያያዘ ሊደርስ ከሚችል የሳይበር ጥቃት ራስዎንና ተቋምዎትን እንዲጠብቁ እንመክራለን።